admin
Wed, 12/18/2024 - 18:03
ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚዎች ጋር ውይይት አደረጉ፤
ሆሳዕና፦ታህሳስ 9/2017ዓ.ም
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚዎች ጋር ተወያዩ።
በውይይታቸውም ምክር ቤቱን እስከታችኛው መዋቅር ለማቋቋም የተደረጉ ጥረቶችን ስራ አስፈጻሚዎቹ በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ምክር ቤቱ ተመስርቶ ስራ ከጀመረ ወዲህ መልካም የሚባሉ ስራዎች መሰራታቸውንም አንስተዋል።
ምክር ቤቱ የሰለጠነ የዴሞክራሲ ባህል እንዲያድግ የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝም ያስታወቁት የኮሚቴው አባላት ፤ምክር ቤቱ ተጠናክሮ እንዲወጣ የክልሉ መንግስትና ገዢው ፓርቲ እያደረጉ ያለው እገዛ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በክልሉ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለመደገፍና በሰው ተኮር የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ለመሳተፍ የተለያዩ ጥረቶች እያደረጉ እንደሚገኙም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።
ስራ አስፈጻሚዎቹ ከዶክተር ዲላሞ ጋር ባደረጉት ውይይት ተከታታይነት ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠና ለምክር ቤቱ አባላት የሚሰጥበት መንገድ እንዲመቻችላቸውና በዞን ማዕከል የጋራ ምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት እንዲከፍት እገዛዎች እንደሚያስፈልጉም አስረድተዋል።
የክልሉ መንግስት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት እያደረገ ያለውን ጥረት ያደነቁት የጋራ ምክር ቤቱ አባላት
በቀጣይም በውይይትና በመነጋገር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም አሳውቀዋል።
ክልሉ ማዕከላዊ አስተሳሰብ እያራመደ የሚገኝ መሆኑንም ያነስቱ የምክር ቤቱ አባላት ለዚህም የጋራ ምክር ቤቱ አንዱ ማሳያ መሆኑን አመላክተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ በበኩላቸው ምክር ቤቱ እስከታችኛው መዋቅር እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ያነሷቸውን ጥያቄዎች በጋራ ለመመለስ እንደሚሰራና ተቀራርቦ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም ስራ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በቀጣይ ለሁሉም አካል እኩል አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ክንፎችን በየደረጃው ማቋቋምና ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ የመፍታት ልምድ እያደገ እንዲመጣ በጋራ መረባረብ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዶክተር ዲላሞ አያይዘውም ከሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በሰላምና በውይይት ተቀራርቦ ለመስራት ብልጽግና ፓርቲ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀው ምክር ቤቱ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
ዶክተር ዲላሞና ስራ አስፈጻሚዎቹ በጋራ በመሆን የጋራ ምክር ቤቱን ቢሮና የስራ እንቅስቃሴም ምልከታ አድርገዋል።
Image
