Skip to main content

ሆሳዕና ፣ህዳር 26/2017ዓ.ምበማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የ2016 ዓም የአፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 የንቅናቄ መድረክ በቡታጅራ ከተማ እየተካሔደ ነው

በንቅናቄ መድረኩ በጤና እና በትምህርት ዘርፍ በሚስተዋሉ ችግሮች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በውይይቱ ማጠቃለያ በሰጡት የስራ መመሪያ ላይ እንደገለጹት በክልሉ በማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ከ1ቢሊየን በላይ ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል።

የማህበረሰብ ጤና መድህን ካለው ጠቀሜታ አንጻር ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል።

በተለያዩ ጊዜያት ከህዝብ የተሰበሰበውን ሀብት ለታለመለት አላማ እንዲውል በማድረግ ረገድ የተስተዋለውን ብልሹ አሰራር ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ ከህዝብ ተሰብስቦ በግለሰብ እጅ ያለውን ገንዘብ ኦዲት በማድረግ ለታለመለት አላማ እንዲውል መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዜጎች ከመከላከል በላይ የሆኑ የጤና እክሎችን ማከም እንዲያስችል የተመሰረተው የማህበረሰብ ጤና መድህን ፕሮግራም ውጤታማ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው እንደገለጹት የክልሉ መንግስት ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ በክልሉ የትምህርት ቤት ምገባ ነው ብለዋል።

ፕሮግራሙ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በመሸጋገር፣የዜጎች የመረዳዳት እና የመተሳሰብ ባህል የሚዳብርበት ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም ጠቁመዋል።

በ2016 ዓም የትምህርት ዘመን የክልሉ መንግስት በመደበው 16 ሚሊየን ብር በጀት ተማሪዎችን የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በ13 ወረዳዎች በ66 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚማሩ ለ54ሺ 671 ህጻናት የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ህጻናት በተገቢው መንገድ ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ በማድረግ ረገድ የትምህርት ቤት ምገባ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት ለትምህርት ቤት ምገባ 20 ሚሊየን ብር ይመድባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

የመጽሀፍት ህትመት ሀብት የማሰባሰብ ስራ ላይ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

የትምህርት ስራ በባህሪው ትውልድ ቀረጻ ላይ ትኩረት ያደርጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዘርፉ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የሁሉንም አካላት የላቀ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልለ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ እንደገለጹት ከትምህርት ሴክተር አንጻር በክልሉ የመማሪያና ማስተማሪያ የመጽሀፍት ላይ ተመስርቶ የቀረበውን ስርዓተ ትምህርት ውጤታማ ለማድረግ የግብዓት አቅርቦትን ማሻሻል እንደሚገባ ተናግረዋል።

መጽሀፍት በሚፈለገው ጥምርታ እና በወቅቱ በፍትሀዊነት ተደረረሽ ማድረግ ለትምህርት ዘርፉ እድገት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

ክልሉ በአዲስ መልክ መደረረጀቱን ተከትሎ ባጋጠመው የበጀት እጥረት ሳቢያ የትምህርት ስርዓቱ እንዳይስተጓጎል መላውን ህብረተሰብ ፣ባለሀብቶችን፣ታዋቂ ግለሰቦችን ፣አጋር ድርጅቶችን እና ሌሎችንም በማሳተፍ ከ326 ሚሊየን በላይ ብር ሀብት ማሰባሰብ ስለመቻሉ ኃላፊው በአብነት ጠቅሰዋል።

በክልሉ በህብረተሰብ ተሳትፎ 1ሚሊየን 391ሺ 143 መጽሀፍት በማሳተም ለ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች እና መምህራን ለማሰራጨት መቻሉን ተናግረዋል።

ለመማሪያና ለማስተማሪያ መጽሀፍት ህትመት ሀብት በማሰባሰብ ረገድ የክልሉ ህዝብ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሉን አቶ አንተነህ አብራርተዋል።

በመማር ማስተማሩ ላይ የሚያጋጥመውን የትምህርት ግብዓት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመረው ህዝባዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቶ አንተነህ ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ እና ውጤታቸውን ለማሻሻል ከሚያግዙ ግብአቶች ውስጥ አንዱ የትምህርት ቤት ምገባ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።

የምገባ ፕሮግራሙ ዋነኛ አላማ የትምህርት ብክነትን፣መጠነ ማርፈድ፣መጠነ መቅረት ፣መጠነ ማቋረጥ እና መጠነ መድገምን በመቀነስ ተማሪዎች በትምህርት ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያግዝም አቶ አንተነህ አብራርተዋል።

Image