Skip to main content

ሆሳዕና፤ታህሳስ፣04/2017ዓ.ም
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ግብር በፈቃደኝነት የመክፈል ባህል እንዲዳብር በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ አደረጃጀቶች ፣ ሲቪክ ማህበራትና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ ግብር የአንድ ሀገር የሠላምና የልማት መሠረት መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገሪቱን በሁሉም ዘርፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ጠንካራ የግብር ስርዓት መዘርጋት ይገባል ያሉት ዶክተር ዲላሞ ግብርን በሀገር ፍቅር ስሜት በፈቃደኝነትና በታማኝነት በመክፈል የክልሉን ልማት ማፋጠን እንደሚገባ ገልፀዋል።
ግብር የመክፈል ልምድ አነስተኛ መሆን፤ የአሰራር ቅልጥፍና ውስንነትና የአመለካከት ችግር ተግዳሮት መሆኑን ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች ጠንካራ ውይይት በማድረግ በክልሉ የታቀደውን ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ በወቅቱ በመሰብሰብ ለህብረተሰቡ ልማቱን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አቶ አሊ ከድር የተጀመረውን ሁለንተናዊ ልማት ለማረጋገጥ የክልሉን ገቢ በውስጥ አቅም ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ቢሮው የታክስ ተገዢነት ለማሳደግ የክህሎት ስልጠናና የተለያዩ መድረኮች በማዘጋጀት የታክስ ከፋዩን ግንዛቤ በመፍጠር የታክስ ተገዢነት ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል።
የታክስ ስወራና ማጭበርበር ድርጊቶች በረቀቀና በተሰወረ መልኩ እየተፈፀመ መሆኑን ገልፀዋል፤ የታክስ ስርዓቱን እየፈተኑ ከሚገኙ ተግዳሮቶች አንዱ በግብይት ወቅት ደረሰኝ ባለመስጠት የሚፈፀም የታክስ ህግ ጥሰት ነው ያሉት አቶ አሊ ሸማቹ ህብረተሰብም ደረሰኝ ባለመጠየቅ የሀገርን ዕድገት እየጎዳ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን የታክስ ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ለልማት ማዋል እንዲቻል የጋራ ጥረትና ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑንም አቶ አሊ ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ የክልል የቢሮ ፣ የዞንና የልዩ ወረዳ ሀላፊዎች ፣ የሀይማኖት አባቶችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
Image